2014 ጃንዋሪ 3, ዓርብ

ድለቃ




ጠርሙስ እያጋጨን
ወይን እየተጎነጨን
ያወራነው ሁሉ ያቀድነው ጠቅላላ
ስለ ዳቦ ቁራሽ ስለ ውሃ አተላ
ስለበደላችን ስለፍትህ ማጣት
ከንቱ ስለጠፋው የሰው ልጆች ህይወት
እስር ስለዋለው ነጻነት ይሉት ሱስ
ዋጋው ስለጠፋ ሰው ስለሚባል ቅርስ
ነበረ ወይ ባክህ? ያወራነው ወሬ
አስታውሰኝ ላስታውሰህ ተዘነጋኝ ዛሬ
ባዶ! ባዶ ጣሳ
ያውም የተበሳ
ባዶ ባዶ ወንፊት
የሚያሳልፍ ምርጊት
ከፊቴ ተቀምጦ
ዝንጋኤ ሞላው ድህነቴ አምጦ፡፡
እውነት እኔና አንተ ወይን ከጨለጥን
ጠርሙስ ከጨበጥን
አንድ መንፈቅ ቀርቶ አንድ ሳምንት ሞላን?
ወይስ ያወራነው
እንዲያ የተከዝነው
ስለህዝቡ ማጣት
ስለሰው መገፋት
ስለፍትህ መጥፋት
ድህነት ተጭኖት መሸነፍን ፈርቶ
በይሉኝታ ብቻ ስለሚኖር ሞቶ
ስለዚህ ሚስኪን ህዝብ ስለዚህ ባተሌ
ስለነዛ መርዛም ስለኒያ አለሌ
አልነበረም ከቶ ወይስ ተሳሳትኩኝ
አንተ ስትደነድን እኔ ኮሰመንኩኝ፡፡
እኔያ እያልኩ ስጠቁም ቅርቤ ርቆብኝ
እንዴት ተቀረጠፍኩ እንዴት ተሸወድኩኝ፡፡
አይደለ አይደለ ወሬያችን ነው ሌላ
ስለሚተኛ ነው ነው ስለሚበላ
የሴቶቹ ዳሌ የመኝታው ምቾት
የአራቱን መናፈቅ የቀለም ቤት ድምቀት
ስለቅንዝር ዓለም ስለፍትዎት ደስታ
ስለዘጠኝ አለም ስለሙሉ እርካታ
ነበር ያወጋነው ብርጭቋችን ሞልቶ
ምላሳችን ታስሮ ህሊናችን ሰልቶ
ነው እንዴ ወዳጄ? ግራ ገባኝ ዛሬ
ድርድር ቦታችንን ብመለከት ዞሬ
በዚህች ቡናኝ ሐገር አቡናኝ በሞላባት
ከድሀ ቀምቶ ሀብታም በኖረባት
ነጻነት በጠማው እስረኛ ነዋሪ
ሌላ አጭር ሰንሰለት የሚያስር ቋጣሪ
ፍትህ በናፈቀው አንጋጣጭ ተበዳይ
የግፍን ተራራ የሚጭን ባናት ላይ
እንዴት ተከሰተ ከቶ እንደምን መጣ
እያልኩ ስደሰኩር እያልክ ስትንጣጣ
የለበስከው ማሊያ መቼ ተቀይሮ
የታፈነን አፋኝ ሆንክልኝ ቀበሮ
የምትገኝ መስሎኝ ከፊት ለተበዳይ
ካሸናፊ መድረክ በቀልክ እንደእንጉዳይ
ለባለድል መዝሙር ለሞላው አጃቢ
አከንፋሹ ሆነህ እብደቱን ጀብጃቢ
ወይንህ ሲጎልብህ የምትጎነጨው
ከፊት ድንገት ወጥተህ ደሀን የምትፈጨው
የፍትህ ናፋቂን ተስፋ የምትቀጨው
ለዛሬ ፍስሐ ለማይዘልቅ ደስታ
ውለህ ለማታድረው ላልገዛኽው ቦታ
ለምትወድቅበት አጥንትህ ተግጦ
ለምትጣልበት ስኳርኽ ተመጦ
ላንድ ቀን ላንድ ዛሬ ነው የተሰለፍከው
የገዳይን ፍትህ ላገር የሰበክከው፡፡
ካዓለም የተማርነው በዘመን ቆይታ
ሌላ ነው ልዩ ነው የእውነት እውነታ
ላሸናፊ መቆም ሆድ ብቻ ይበቃል
ተሸናፊን ማገዝ ወኔን ይጠይቃል፡፡
2005-18/4/2006