2013 ሜይ 3, ዓርብ

ባለጸጋ ሰው

በምሬት ተሞልተው በአውድ ባደባባይ ሰዎች ይዘልፋሉ
በጓዳ ጎድጓዳ ሌቦች ተደራጅተው ደሀ ይዘርፋሉ
መግቢያ የጨነቀኝ መሸሸጊያ አጥቼ ቆሚያለሁ ካውላላ
ከተደበቀ እውነት ከሰዎች አሰሳ ከእልፍ ምላስ ኋላ
ማነው እኔን ያየ? መልኬን ያስተዋለ ነውሬን የገለጠ
ማነው ሀብቴን ያየ? ከተሸሸገ ሀብት የኔን የመረጠ
ኑልኝ ነጣቂዎች ደሃን አትምዝብሩ ከኔ አለ የላቀ
ዝቃችሁ ማትገፉት የተሸሸገ ሀብት ለአይን የረቀቀ
የያዝኩት በጽኑ ከሌሎች ጠብቄ ከነፍሴ እኩሌታ
አለላችሁ ሀብት አለላችሁ ገንዘብ ለጊዜ ያልተረታ
ሰብ የሚባል ሀውልት ሰው ይሉትን ቅርስ ያጣችሁት ከቶ
እኔ ዘንድ ተኝቷል እናንተ ውስጥ ሞቶ፡፡
ኑልኝ ዘላፊዎች ተጯጯኹ ደግሞ አዲስ ስም ሰይሙ
‘ሰው’ ከመባል ውጪ ለሰው እውነት የለም የሚከብር ስሙ
ስደቡት ይኽን እኔ ‘ሰው’ በሉት ደግማችሁ
ከሰው ተለይቷል ጋርዮሽ ላይ ቆሟል እናንት ሰልጥናችሁ፡፡
ዛሬም “እኛ” ይላል ብቻውን ካውላላ ቆሞ ተገትሮ
አይታችሁ አታውቁም እንዲህ ያል ደንቆሮ::
ተዉ አትድከሙ አይጥበብ ቴራሱ አትሙሉ አደባባይ
ስድቡን የሚጓጓ ስሙ የናፈቀው ቆሟል ካይናችሁ ላይ
ተዉ አትባክኑ ዝርፊያውን አቁሙ ደሀ አይርገማችሁ
ከሁሉ የከበረ ሀብታም ባለጸጋ ሰው እዚህ አለላቹ፡፡
                             26/11/2004