2013 ጁላይ 24, ረቡዕ

የይታገሱ መስኮት: ስለራስ የሳሉትን ምስል ማምለክ እና ራስ የሳሉትን ስዕል መፍራት

የይታገሱ መስኮት: ስለራስ የሳሉትን ምስል ማምለክ እና ራስ የሳሉትን ስዕል መፍራት

ስለራስ የሳሉትን ምስል ማምለክ እና ራስ የሳሉትን ስዕል መፍራት



ሁለት አደገኛ ነገሮችን አውቃለሁ፤ ስለራስ የሳሉትን ምስል ማምለክ እና ራስ የሳሉትን ስዕል መፍራት፡፡ ሁሌ ባየኋት ቁጥር የምትገርመኝ ስዕል አለች፡፡ ስዕሏ መስታወት ፊት የቆመች ድመትን ይዟል፡፡ በመስታወቱ ውስጥ ያለው ምስል ግን የድመቷ ሳይሆን የአንበሳ ነው፡፡ አንዳንዴ አካባቢያችንን ስናስተውል ከሆኑት በላይ ለራሳቸው ስዕል ታላቅነትን የሰጡ ለዛም የተሳሳተ ምስል የሚንበረከኩ በርካቶች ናቸው ፡፡ በፖለቲካውም፣ በመንደሩም፣ በመስሪያ ቤቱም ሆነ በጓደኝነቱ እነዚህን ማግኘት አይከብድም፡፡ እነዚህ ሰዎች “እኔ” ከሚል ቃል የበለጠ የሚያውቁት የሌለ ይመስላሉ፡፡ የሁሉም ነገር ባለቤት እና ፈጣሪ አድርገው ራሳቸውን ያስባሉ፡፡ ሲመስላቸው እነሱ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ምድር እንኳን ምህዋሯን ጠብቃ እንዴት ልትዞር እንደቻለች ይገርማቸዋል፡፡ ያንንም መስማት እሱንም መናገር አይሆንላቸውም፡፡ ሊያወሩም ሆነ ሊናገሩ የሚፈልጉት እነሱ ስላበረከቱት አስቷጽዖ እንጂ ስለሌሎች አበርክቶ አይደለም፡፡
ብዙም ርቀን አንሂድ፤ በቀኝም ሆነ በግራ የተሰለፉትን ፖለቲከኞቻችንን ማየት በቂ ነው፡፡ የነገሮች ሁሉ ቁልፍ የሆኑ መሆኑን ሊነግሩን እና ሊመክሩን ይነሳሉ፡፡ እነሱ ጋ ፈጽሞ መሳሳት ይሉት ታሪክ የሌለ ያስመስሉታል፡፡ የመፍትሄዎች ሁሉ መፍትሄ ከነርሱ ውጪ እንደሌለ ይነግሩናል፡፡ ለመናገር እንጂ ለመስማት ጆሮ የተፈጠረባቸው አይመስሉም፡፡ ስለራሳቸው የሳሉት ስዕልን ተጠራጥረው አያውቁም፡፡ በነሱ መፍትሔ ሐገር የረጋ ህዝብ የተጋ ይመስላቸዋል፡፡ የሚለኩት እና የሚመትሩት እነሱ ካሉበት አቅጣጫ ብቻ ስለሆነ ልዩነቱን መረዳት አይቻላቸውም፡፡ ምናልባት የቆሙበት አላማ የተሳሳተ ሊሆን እነደሚችል ፈጽሞ ማሰብ አይሹም፡፡ ከእውነታው ጋር ሲፋጠጡ ማጥፊያ እንጂ መታጠፊያ መንገድ የላቸውም፡፡
ይህ አይነት ስለራሳችን የተጋነነ ስዕል መስጠት ከአደገኛ በላይ አደገኛ ነው፤ የሰናዖር ውድቀትን ያመጣል፡፡ አለአግባብና አለአቅም አየር ላይ መንሳፈፍ ከእውነተኛው ማንነት ጋር መፋጠጥ ሲመጣ ማረፊያ ያሳጣል፡፡ በራስ መተማመን ደግ ነገር ነው፤ በራስ ማመን (ራስን ማምለክ) ግን ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አንዳንዶች እጃቸው ላይ ያለው ነገር አስተማማኝ እና የማይናድ ይመስላቸዋል፡፡ እውቀት ማለት ያልታወቀ ነገር እንዳለ ማወቅ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም መጠርጠሩ ይበጃል፡፡ የዛሬው ማወቃችን ነገ አላዋቂነት እና የተሳሳተ ሊባል እደሚችል ማመን ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ማመንም ልክ ያስፈልገዋል ከእኔ ርዕዮተ አለም ውጪ ላሳር፣ ከኔ ሃይማኖት ውጪ ዉጉዝ፣ ከኔ ዕውቀት ውጪ ድንቁርና ማለት ራስን ማምለክ ነው፡፡ ትንሽም ቢሆን አቋማችንን መጠራጠር የእድገት እና የእውነት በር ነው፡፡
ሁለተኛው አደገኛ ነገር የራስን ምስል መፍራት ነው፡፡ ይሄኛው ደግሞ በጣም የከረረ ጥርጣሬና ፍርሐት ነው፡፡ ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ያጫወተኝን አንድ ታሪክን ላስቀድም፡፡ በአንድ መንፈሳዊነት በበረታበት ገዳም ውስጥ የነበሩ መነኩሴ ሰይጣን ሁልጊዜ ከጸሎት ሊያስታጉላቸው እንደሚታገል ያምናሉ፡፡ እያንዳንዷም ቀን እንዳትባክን በመጠንቀቅ በማነጋጊያው ላይ ለሚጸለየው ጸሎት ማልደው ጨለማው ሳይወግግ ወደቤተክርስቲያን ያቀኑ ነበር፡፡ አንድ ቀን ቀድመው ተነስተው ከለሊቱ በአስር ሰዓት ወደ ቤተክርስቲያን ያመራሉ፡፡ በበአታቸው እና በቤተክርስቲያኑ መካከል አንዲት ጠባብ ድልድይ አለች፡፡ እዚች ድልድይ ጋ ሲደርሱ ከድልድዩ አቅጣጫ አንድ ጠቆር ያለ ነገር ሲንቀሳቀስ ተመለከቱ፡፡ አባ አማተቡ፤ ያ ነገር ግን አልጠፋም ባለበት ረጋ፡፡ አባ መቁጠሪያቸውን አውጥተው ባሉበት ቆመው ጸሎታቸውን ጀመሩ፡፡ ያሰቡት ሰይጣን ግን ከቦታው አይንቀሳቀስም፡፡ እሱም የድልድዩ መጨረሻ ላይ እንደቆመ ነው፡፡ አባ ውጊያቸውን በማፋፋም መከላከላቸውን አጠናከሩ፡፡ ከማለዳው ጸሎት ያስቀራቸውን ሰይጣን በትጋት ባሉበት ቦታ ቆመው ሳይሸሹ ተዋጉት፡፡ አባ በቆሙበት ጨለማው እየለቀቀ የማለዳውም ጸሎት እያለቀ መጣ፡፡ በብርሐኑ አተኩረው ሲያስተውሉ እሱም እንደሳቸው ከፊቱ የቆመውን ሰይጣን በጸሎት እየታገለ ያለውን የገዳሙን መነኩሴ ተመለከቱ፡፡    
ከመጠን ያለፈ ተጠራጣሪነት ከመዳረሻችን ያዘገየን ወይም ያስቀረን በርካቶች ነን፡፡ ሁሉንም እኔን ለመበደል የተደረገ እኔን ለማዋረድ የተነገረ ነው የምንል ከሆነ አደገኛ ነው፡፡ ይህ ከመጠን በላይ የሆነ መጠራጠር ባልተረጋገጠና እራሳችን በሰራነው ስዕል እየታገዘ የበታችነት ስሜታችንን በማባባስ የቆቅ ኑሮ እንድንኖር ያደርገናል፡፡ እከሌ ይጠላኛል እከሌ ያጠቃኛል ብሎ ማሰብ ሰላም አይሰጥም፡፡ በተለይም ዉሱንነት ላለበት ሰው ራሱን ጠብቆና ደብቆ ላይኖር ነገር ህሌናን ይረብሻል፡፡ ይሔኛው ዘር ይንቀኛል ስለኔ እንዲህ ብሎ ያስባል የሚል የከረረ አመለካከት ደግሞ የባሰ ህዝብን ይበጠብጣል፡፡ በርግጥም እንዲህ ያለ የሐሳብ መረበሽ ያለባቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በስነ አምሮም ጥናትም ራሱን የቻለ በሽታ መሆኑ ታውቆ ህክምና ይሰጣል፡፡ ችግሩ ግን እነዚህ ሰዎች ህመም መሆኑን አያምኑም ፡፡ ጤነኛ መስለው በየቢሮው በኃላፊነት ተቀምጠዋል፡፡ በየመድረኩ ንግግር አዋቂ ተብለው ጥላቻን የሚሰብኩ ህዝብም የሚያዳምጣቸው ናቸው፡፡
እንደነዚ አይነት ራሳቸው የሳሉትን ምስል የሚፈሩ ተጠራጣሪዎች ሊደርሱበት የሚያልሙትን ነገር ከመያዝ ይልቅ በህሌናቸው ከሳሉት ስዕል ጋር ሲላፉ ዕድሚያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ የበዛ ጥርጣሬ ሰላም የለውም፣ በአካባቢው ለሚገኙ ሌሎችም ሰላም አይሰጥም፡፡ እያንዳንዷን ቃል እየሰነተቁ እንዲህ ሊለኝ ፈልጎ ነው እያንዳንዷን የታሪክ ሰበዝ እየለቀሙ ዛሬም እንዲህ ሊያደርጉን አቅደው ነው ማለት እረፍት ያሳጣል፡፡ የዚህ አይነት ሰዎች ጥፋታቸው የትዬ ለሌ ነው፤ ፈሪ ሲደነብር ጀግናን ያስንቃል፡፡
ሐሳቤን ልጠቅልል ለራስ የሰጠነውን ስዕል በማምለክ እና ራስ የሳሉትን ምስል በመፍራት መካከል ያለው ልዩነት በከንቱ መወጠር እና አጉል መኮስመን ብቻ ነው፡፡ በተረፈ ሁለቱም የአንድ ሸማ ሁለት ጥለት መልክ ናቸው፤ የውድቀት ቁልቁለት፡፡