2013 ማርች 26, ማክሰኞ

እውቀትን መፈለግ

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አሜሪካ በጃፓን ላይ ሁለት አውቶሚክ ቦንብ ጣለች፡፡ በርካታ ሕዝቦች ከመቅጽበት እቺን አለም ተሰናበቱ፡፡ በጊዜው የጃፓን መሪ ሐገራቸው ላይ ጥቃት እንደተሰነዘረ ዜናው ደረሳቸው፡፡ ሁኔታው ታላቅ መርዶ ነበር ፡፡ ቅድሚያ የጠየቁት ነገር አንድ ነው “ምን ያህል መምህራን የሚተርፉ ይመስላችኋል?” ፡፡
በርግጥ በእንዲህ አይነት ጅምላ ጨራሽ ጥቃት ውስጥ መምህርን መርጦ የሚተው ተአምር የለም፡ ይኽ ይጠፋቸዋል ብለን አንገምትም፡፡ ሆኖም ስለሔደው ከማሰብ በላይ ስለሚመጣው ማሰብ የባለተስፋዎች አለም መሆኑን ቢረዱ እንጂ፡፡ ግን ለምን መምህር? ታላላቅ ባለህልሞች እና ሳይንቲስቶች፣ ቀመር ፈጣሪች እና ተአምር ሰሪዎች ባሉባት ሀገር እኒህን ሰው መምህር እንደምን እራባቸው?
እንዲህ መስለኛል፤ ጃፓንን እዚህ ግቢ ከማትባልበት ሥፍራ አንስቶ ኃያል እና ታላቅ ያደረጋት እውቀት ፈላጊነት እንጂ እውቀት እራሱ አደለም፡፡ ይሔንን ደግሞ የሰጣት መምህራኗ ናቸው፡፡ እውቀት ለአንድ ውስን ነገር መፍትሔ ይሆናል፡፡ እውቀት ፈላጊነት ግን በማይቋረጥ ሂደት ውስጥ ችግሮችን እየፈቱ ምስጢሮችን ገሀድ እያወጡ መኖር ነው፡፡ በሌላ አባባል አንድ ኢንጂነር ህንጻ  ሰርቶ የመኖሪያ ችግርን ያቃልላል ለነዋሪው አኗኗሩን ግን ሊያሳየው አይቻለውም፡፡ አንድ ዶክተር በሽታን ያክማል እንጂ ጤናን አይጠብቅም፡፡ በፎቅ የመኖርን ስርአትም ሆነ ጤናውን ተከታትሎ የመጠበቅ ልማድ የእያንዳንዱ ሰው ፈንታ ነው፡፡ ደግሞም ሁለቱም የዛሬን ችግርን ቢያቃልሉ እንጂ ለነገው ችግር መፍትሔ አይሆኑም፡፡ ይሄን እውቀት ፈላጊነትን ሊሰጥ የሚችለው መምህር ብቻ ነው፤ መምህር ባለበት እውቀት መፈለግ ብርቱ ትሆናለች፡፡
እውቀትን መፈለግ ስትሰፋ ድንቁርና፣ ለኔ ይድላኝ ማለት እና ከኔ በላይ ማን አለብኝነት ስፍራ አይኖራቸውም፡፡ ህንጻዎችን በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ሊገነቡና ከተማ በተንቆጠቆጡ የድንጋይ ጫካ ሊሞሉ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ህንጻዎችን የኔ የሚላቸውና የእውቀት ፍሬ መሆናቸውን የሚረዳ የለማ ባለ አዕምሮ ህዝብ ከሌለን ግን እንደ ሔሮሽማ እና ናጋሳኪ ለመውደማቸው ከተሰሩበት ጊዜ እጅግ ያነሰ ሰአታት ብቻ ነው የሚወስደው፡፡
ዋናው ጭብጣችን እውቀትን መፈለግ ነው፡፡ ጃፓን ከዛ ሁሉ መአት ተርፋ አሁንም ታላቅ ሆና እንድትታይ ያደረጋት ምስጢር ይኽው እውቀትን ፍጊነቷ ነው፡፡ አንድ ህዝብ እውቀትን መፈለግ በመምህሩ ይማራል፡፡ ከትምህርት ቤት ከወጣ በኋላም ግን መምህሩ በሰጠው ዋና መሳሪያ አማካይነት እውቀትን ሲያስስ ይኖራል፡፡ ይህ መሳሪያ ደግሞ ንባብ ነው፡፡ ከንባብ ውጪ ሆነ ህዝብ ደካማ ነው፡፡  በተለይ በዚህ መረጃ ኃይል በሆነበት በዘመነ-ልዑላዊነት ውስጥ የማያነብ ህዝብ ያላት ሀገር የመጥፊያዋን ጉድጓድ እየቆፈረች ነው ማለት ይቀላል፡፡
እውቀትን የማያስስ ንባብን የሚጠላ ባለስልጣን የከበባት ሀገር መከራዋ ረዥም ነው፡፡ ዛሬ ያለንበትን ችግር ሁሉ መልስ ሚሰጡ በርካታ አቋራጮችን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ድልድዮችን ህንጻዎችን እርሻዎችን መንዶችን የሚሰራ ድርጅት ከፍለን ከውጭ እናስመጣው ይሆናል፡፡ የተሰሩትን ስራዎች ምንገለገልባቸው ግን እኛው ነን፡፡ ደግሞም ለዛሬ ችግራችን መፍትሔ ሊሆኑ እንጂ ለነገው ችግራችን ዋስትና መሆን አይችሉም፡፡ ስለዚህም እውቀት አሳሽ፣ ንባብ ወዳድ ህዝብ ያስፈልገናል፡፡  
ይቀጥላል    

2013 ማርች 15, ዓርብ

የአያቴ ሐገር እንግዳ


ጊዜው ትንሽ ቆየት ብሏል፡፡ ለበርካታ ጊዜ አዲስ አበባ ሲመላለስ የማውቀው አያቴ እርጅና ተጭኖት ብቅ አልል ስላለ በዛውም ገጠሩን ማየት ስላማረኝ ሁለቱንም ልሳለማቸው ብዬ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ከዚህ ቀን አስቀድሞ ነፍስ ካወቅሁ በኃላ ማለቴ ነው እንዲህ ያለ ገጠር ውስጥ ገብቼ አላውቅም፡፡ በዛ ወቅት የመንግስት መገናኛ ብዙሀን እስከዛሬ የሐገሪቱን የጥቅም እፍታ ለብቻው ሲያግበሰብስ የነበረው ክልል ይህ እንደነበር ስለሚያወሩ የነበረኝ ምናባዊ ስዕል ትልቅ ነበር፡፡
አባይን ከተሸገርኩ በኋላ የማየው ትዕይን ግራ አጋባኝ፡፡ ያደፈ ጥብቆ ያደረጉ፣ ደሳሳ ጎጆዎቻቸው አካባቢ የከሱ የገረጡ ህጻናት እና ከብቶች የሞሉባቸው ጉስቁልናቸው እስከዛሬ ካየኋቸው ኢትዮጵያውያን የከፋ ህዝቦች ነበር የሚታዩኝ፡፡ የቆርቆሮ ቤት መኖር ለአካባቢው እንደስልጣኔ ተቆጥሮ ባለቆርቆሮ ቤቱ መንደር ይባላል ፡፡ በጉዞዬ ውስጥ በየማኃሉ የማገኛቸው ከተሞችን “ከተማ” ያልኳቸው ሌሎች ስላሏቸው ብቻ ነው፡፡ በዛ ላይ አንዱ ከአንዱ ያለው ርቀት ያስደነግጣል፡፡ በትንሹ ከአዲስ አበባ 200 ኪ.ሜ በማይሞላው ርቀት ላይ የምትገኘው አዋሳ እስክንደርስ ድረስ ስንት ትንንሽ ከተሞችን እንደምናይ ሳስበው ይህ ክልል አሳዘነኝ፡፡ 'ገጠሬነትን ክብር አድርጎ ራሱን ሲበላ የኖረ መሆኑን የሚነግረው አጥቷል ማለት ነው' ስል አሰብኩ፡፡ ባህርዳር ስደርስ ተስፋ ቆረጥኩ . . . ብዙም የሚጋነልላት አልሆነችልኝም፡፡ ያኔ በነበረው ህግ መሰረት አንድ የህዝብ ትራንስፖርት ወዲህ ሲመጣ ማደሪያውን የሚያደርገው የግድ ባህርዳር ላይ ነበር፤ ከመሸ መጓዝ አይፈቀድም፡፡
ከመኪና እንደወረድን ዳግመኛ ደብረታቦር የሚሄድ ሎንቺና ፈላልገን አገኘንና ከመሸ ገባን፡፡ በስም እና በዘፈን ብቻ አውቃቸው የነበሩትን አሞራ ገደል፣ ደንቢያ፣ ወረታን “በዚህ ነው” “ይሄ ነው” ባሉኝ ቁጥር እየተደነቅኩ እና እየተሸማቀቅኩ ነበር አጓጓዜ፡፡ ያኔ ነው “ለአፍ ዳገት የለውም” ብሂል የገባኝ፡፡ አሁን እነዚህ የደቀቁ እና የፈራረሱ ከተሞች ናቸው ለዘፈን በቅተው ድፍን አዲስ አበቤን ሲያምሱት የከረሙት? አልኩኝ ለራሴ፡፡ (በወቅቱ በርካታ የባህልና ዘመናዊ ሙዚቀኞች ጎጃምን እና ጎንደርን እየጠቀሱ ከከተማም አልፈው ጎጥና መንደሩን፣ ሳርና ቅጠሉን እያነሱ እንዲዘፍኑ የተገደዱ ይመስሉ ነበር) እንደውም ሳስበው ምናልባትም ለክልሉ እንዲህ ጠላት ያበበት ዘፈኖቹ ይመስሉኛል፡፡ ያልተመቸውን የሌለውን እያቆለጳጰ የዘረፈ አስመስለው ያቀረቡት ለማለት ከጅያለሁ፡፡


ደብረታቦር፡- አስገራሚ ነው! ከአንድ መቶ ሃምሳ አመታት በፊት በከተማነት የምትታወቅ ቢሆንም ዛሬ መንደርነት ትልቅ ክብር አለው፡፡ ድንጋጤዬ እየገዘፈ ነበር የሔደው፡፡ ሁለት ቀን ከገጠር ዘመዶች በቅሎ ይዘው እንዲመጡ መልዕክት ለመስደድ በገበያ ውስጥ ሰው ስናፈላልግ ቆየን. . . .፡፡ ሰው አግኝተን መልክታችንን ከነገርን በኋላ ግማሹን መንገድ ለማጋመስ ቀድመን ተነሳን፡፡ ካረፍንበት ሆቴል ልንወጣ ስናኮበኩብ አብረውኝ ከአዲስ አበባ የመጡት ሐገሩን ጠንቅቀው የሚያውቁት ወዳጆቼ የምንነግርህ ነገር አለ ብለው በስርአት እንዳዳምጣቸው ጠየቁኝ፡፡ 
“የሔውልህ ከዚህ በኋላ በምንም አይነት ማንም ሰው ስምህን ቢጠይቅህ እከሌ ነኝ አትበል፡፡ የማን ዘመድ ነህም ብትባል አትናገር” አሉኝ፡፡
ግራ ተጋባሁ. . . “ለምን?”
“ነገርንህ በቃ! ሲያነጋግሩህ እኛ መልስ እንሰጣለን፤ አንተ ቀድመህ መልስ አትስጥ ብቻ”
ምን እየተደረገ ነው ያለው? ግራ መጋባቴ ጨመረ . . . ከአዲስ አበባ አምኛቸው የመጣሁት እነሱን ነው፡፡ ሐገሩንም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ የሩቅ ቢሆንም ዝምድና ሳይኖረን አይቀርም፡፡ ሆኖም ጊዜው አስተማማኝ አይደለም፡፡ ምንም የርስ በርሱ ጦርነት ከተጠናቀቀ ሰባት ዓመት ቢያልፈውም በየመንገዱ የተቃጠለ ታንክ እና የጦር መኪና ማየት ከብርቅ የሚቆጠር አይደለም፡፡ በዛ ላይ ሰዉ ሁሉንም በጥርጣሬ ሚያይ ስለሚመስል ባይተዋርነትን ያገዝፋል፡፡ ባጠቃላይ ሁኔታው ሁሉ ስጋቴን ሚጨምር እንጂ የሚያቃልል አይደለም፡፡
በዚህ አይነት ስሜት ውስጥ መቆየት አልፈለኩኝም፤ ጥያቄዬን አጠንክሬ ገፋሁበት፡፡
“ይኽውልህ የአካባቢው ሰው ማንን እንደሚጠላ እና ከማን ወዳጅነት እንዳለው አይታወቅም፡፡ አንተ ደግሞ ለሐገሩ እንግዳ ነህ፤ አይደለህም አንተ የትኛውንም ጸጉረ ልውጥን ደግሞ በቀላሉ ማወቅ ይችላሉ”
“እና?” ለጥያቄዬ በቀጥታ መልስ የሚሰጠኝ አላገኘሁም፡፡
“የአንተን አባት በቀላሉ ማንም ሰው የሚያውቀው ነው”
“ታዲያ ይሔ የምትሉኝ ጉዳይ ካባቴ ጋር የሚያገናኘው ምን ነገር አለ፡፡ ደግሞም አባቴ ከሞተ ሃያ ዓመት ሊሆነው ነው፡፡ ምንድን ነው ችግሩ?”
“አባትህ ጋ አይደለም ችግሩ የሚኖረው፡፡ አባትህ ከዚህ ሀገር ከወጣ ራሱ ሠላሳ ዓመት አልፎታል”
“የምትሉኝ አልገባኝም በግልጽ ያለውን ችግር ማወቅ ይኖርብኛል” አልኳቸው፡፡
“:ይሔውልኽ! ችግሩ አያትህ ጋር ነው”
“በግልጽ ንገሩኝ ምንድን ነው ችግሩ?”
ሁለቱም እርስ በርሳቸው ተያዩ. . .


2013 ማርች 13, ረቡዕ

እንዲህ ማሰቤን እንዲህ ላጽና


ው ሆኖ መፈጠር ለማሰብ ነው የሚሉ አሉና መስማማቴን ገልጬ ልንደርደር፡፡ መስማማቴ ግን ከራሴ ጋር ጠብ የሌለው /absolute/ ይደለም፡፡ የራሴን ሐሳብ አለመስማማቴ በራሱ ሁሌ አዲስ መሆኔን ያመለክትልኛልና እወደዋለሁ፡፡
አንዴ ጋሽ ስብሐት መድረክ ላይ ተቀምጦ በባዶ ሜዳ ጥርስ መንከስ ልማድ ከሆነባቸው ሰዎች መካከል አንዱ “በአንዱ መጽሐፍህ ላይ ሞትን የጭንቅ መሹለኪያ አድርገህ አክብረህ ትገልጸዋለህ. . . .ገጸ ባህሪህን በስሙኒ ገመድ ትሰቅላለህ፡፡ በሌላ አቅጣጫ ሞትን ረግመህ ከሞት የሚሸሹ ሰውን ታሞካሻለህ፡፡ ጋሽ ስብሀት በአንድ ጉዳይ ላይ ራሱ መስማማት ያቃተህ ይመስለኛል፡፡ አንተ ከየት ነህ?” ሲል ጠየቀው፡፡ የጋሽ ስብሐት መልስ አጭርና የማያሻማ ነበረች፡፡ “አሹ. . . .! (ደግ አደረግኩ እንደማለት) ድሮስ ቢሆን እኔ ስብሐት ‘ዳይናሚክ’ ነኝ፡፡ በትናንት ሐሳቤ ላይ ዛሬ ትፈልገኛለህ?” 
እውነቱን ነው ስብሐት፤ የሰው ልጅ ባለበት ቦታ የማይንቀሳቀስ ከነበረበት ሐሳቡ የማይለወጥ ከሆነ ሞቷል፣ አሊያም የእድገት ደረጃዎቹን አጉል ቦታ አቁሟል ማለት፡፡ ሰዎች የሰዎችን ሐሳብ እና እምነት ማክበር የሚችሉት በነሱ ውስጥ ያለውን ተቀያያሪነት /ዳናሚዝም/ን በቅጡ መረዳት ሲችሉ ነው፡፡ አሊያ በአለም ላይ አንድ እውነት እና እንድ እምነትን ለማሰልጠን ሲሉ አለምን ሲያተራምሱ ይኖራሉ፡፡ የፖለቲከኞቻችን ትልቁ ችግርም ይህ ነው፣ እነሱ ከቆሙበት አስተሳሰብ ውጪ ያለን ሁሉ ጠላት አድርገው መፈረጃቸው፡፡  
በወዳጅነት፣ በስራ አጋርነት፣ በጉርብትና ወይም በሌሎች ግንኙነታችን ውስጥ ያለንን አኗኗር የተረጋጋ እና መልክ ያለው ለማድረግ በእኛ ውስጥ ያለውን የሐሳብ እና የእምነት ተቀያያሪነትን መገንዘብ ጠቃሚው መንገድ ነው፡፡ በሌላ አባባል ዛሬ በሐሳቡ ያልተስማማን ሰው ነገ ሊለወጥና እኛ እውነት ነው ብለን ባሰብነው አቅጣጫ ሊቆም የሚችል መሆኑን በማመን እድልና ጊዜ ልንሰጠው ይገባል፡፡ እናም እንዲህ ማሰቤን ለማጽናት የኔን ተለዋጭነትንም በማመን ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሄንን ሐሳቤን ደግሞ ነገ ልንደው እችል ይሆናልና፡፡
እረ ሲጀምርም እንዲህ ብዬ ለመጻፍ አልተነሳሁም ነበር፡፡ እንዲህ ሆኖ አለቀ እንጂ፡፡
27/6/2005