2013 ኤፕሪል 27, ቅዳሜ

ባለጸጋ ሰው



በምሬት ተሞልተው በአውድ ባደባባይ ሰዎች ይዘልፋሉ
በጓዳ ጎድጓዳ ሌቦች ተደራጅተው ደሀ ይዘርፋሉ
መግቢያ የጨነቀኝ መሸሸጊያ አጥቼ ቆሚያለሁ ካውላላ
ከተደበቀ እውነት ከሰዎች አሰሳ ከእልፍ ምላስ ኋላ
ማነው እኔን ያየ? መልኬን ያስተዋለ ነውሬን የገለጠ
ማነው ሀብቴን ያየ? ከተሸሸገ ሀብት የኔን የመረጠ
ኑልኝ ነጣቂዎች ደሃን አትምዝብሩ ከኔ አለ የላቀ
ዝቃችሁ ማትገፉት የተሸሸገ ሀብት ለአይን የረቀቀ
የያዝኩት በጽኑ ከሌሎች ጠብቄ ከነፍሴ እኩሌታ
አለላችሁ ሀብት አለላችሁ ገንዘብ ለጊዜ ያልተረታ
ሰብ የሚባል ሀውልት ሰው ይሉትን ቅርስ ያጣችሁት ከቶ
እኔ ዘንድ ተኝቷል እናንተ ውስጥ ሞቶ፡፡
ኑልኝ ዘላፊዎች ተጯጯኹ ደግሞ አዲስ ስም ሰይሙ
‘ሰው’ ከመባል ውጪ ለሰው እውነት የለም የሚከብር ስሙ
ስደቡት ይኽን እኔ ‘ሰው’ በሉት ደግማችሁ
ከሰው ተለይቷል ጋርዮሽ ላይ ቆሟል እናንት ሰልጥናችሁ፡፡
ዛሬም “እኛ” ይላል ብቻውን ካውላላ ቆሞ ተገትሮ
አይታችሁ አታውቁም እንዲህ ያል ደንቆሮ::
ተዉ አትድከሙ አይጥበብ ቴራሱ አትሙሉ አደባባይ
ስድቡን የሚጓጓ ስሙ የናፈቀው ቆሟል ካይናችሁ ላይ
ተዉ አትባክኑ ዝርፊያውን አቁሙ ደሀ አይርገማችሁ
ከሁሉ የከበረ ሀብታም ባለጸጋ ሰው እዚህ አለላቹ፡፡
                             26/11/2004

ኮከብ ነህ ርችት?

በዘመን የማትፈርስ በጊዜ ማትጠፋ
ጥበብ ሲሉኽ ማትጠብ ሲሉ እማትሰፋ
በህያው ሰማይ ላይ ጸንተህ የምትቆም
እኩል የሚገለጽ ብርሀንህ ላለም
ነህ ወይ ተወርዋሪ ነህ ወይ ያጥቢያ ኮከብ
የማታከራክር በሰማያት ክበብ
ንገረኝ በሞቴ ምንድነህ አነንተ ሰው
ላንድ ቀን ቢሆንም ቀኔን አታምሰው፡፡
ከሰሜን ከደቡብ ከምስራቅ ወይ ምራብ
ሊያይኽ ለሚፈልግ ማንህን ለሚራብ
እኩል ትታያለህ እንደኮከብ ሁሉ?
ወይስ መርጦ አቅጣጫ ይታያል ይበራል
                     የብርሀን ጸዳሉ?
በጊዜ በጩኽት በስሜት በረብሻ
በኮከብ ናፋቂ በሰዎች ጥቅሻ
ኮከብ እንድትመስል የተሰራኅ ብርሀን
ከቀናት በኋላ ጮራኅ ሚኮሰምን
ኮከብ ነኽ ወይ ሌላ አርቴፊሻል ነገር?
እውነትህን ግለጥ ሰው አታደናግር
ትሆን ወይ ርችት የበአል መድመቂያ
ከቀናት አንዱን ቀን በተለይ ማሞቂያ
ሰው እንደወደደው ቀለሙን ቀብቶ
በተኳሹ መሻት በተኳሹ ብልሐት 
                         ሽቅብ ከላይ ወጥቶ
ሲፈልግ ነጭ ኮከብ ሲፈልግ ዘንባባ
ሆኖ እንደሚታይ ወጥቶ እንደሚገባ
ትሆን ሆይ ሺህ ቀለም ግራጫ ቀይ ጥቁር
ሰማያዊ ደማቅ አረንጓዴ ነገር
ሐምራዊ  ብርቱካን ቢጫ ወርቀ ዘቦ
ሰው አፉን ከፈተ ማንህን ተርቦ
ምንድነህ ተጠየቅ ማነህ ማን እንበልህ
እዩኝ የምትለን ካናት በላይ ወተህ
በሆታ ጫጫታ የነገስክ ከሰማይ
አንተ ብርሓንማ ኮኮቦችን መሳይ
ፊናህን ለይልን ታሪክህ ይተርተር
ኮኮብ ነህ እርችት ያ ዶሴህ ይበጠር
በጊዜ ምጣድ ላይ በስለህ እስክትመጣ
ከኮኮብ ከርችት አይኖርህም ዕጣ
                        27/12/2004

ደጅ ያደረ ልብ



የልጅነት ህልሜ ጠይሞ መጥቆርሽን ባየው በመልክሽ
ነፍስ አውቄ በዕውን አይኔን ገልጬ ባይሽ
ከፍቅር በቀር ከውስጤ የሚወጣኝ ፍላቂ
አጣሁ በውስጤ ትርጉሙን የመውደዴን ድቃቂ
ከማህጸንሽ በቅዬ ካንቺነትሽ ስር ብገኝም
በስምሽ ስም ገዝቼ ባንቺነትሽ ብጠራም
ቡራኬሽ ባይኖር በላዬ የ“እደግ” ምርቃት ቱፍታሽ
ባትረግሚኝም ቅሉ መኖሬ በዕጆችሽ ጣት ስታሽ
ፍቅሬ ጎመዘዘኝ እናቴ “እማማ” ያልኩሽ አቃረኝ
መውደድሽ ሬት ማቀፍሽ የሾኽ ሆኖ ተሰማኝ::
“ሰው ቦታን ይቀድሳል ቦታ ደግሞ ሰውን ይቀድሳል”
ይሉ ብሒል ጠፋኝ እና አግኝቶ ማመስገንን
ጀረጀርኩ ደጅሽ ላድር ወለለት ባይኖረው ድምጼ
ከጆሮ ደርሶ ባይገባ የእዬዬ ቅላጼ
“እሹሩሩ” መባሉ ቀርቶብኝ በልጅ ወግ መባበሉ
መቅለጥ መቅበጤ ቆይቶ “ስመኽኝ ውጣ” መባሉ
በወጉ ድምጼ ተሰምቶ ከደፍሽ ወድቄ ባደርኩ
የኽው ስልሽ ብተሰሚኝ ባለመስማትሽ ባላዘንኩ::
እናትዬ!
መውደዴ ኪሳራ ብቻ ሲሆን ማፍቀሬ ግርጥጫ
በምን ልታገስ መኖርን በጉስምት በንቅፍት ቁንጥጫ?
አግማስሽ ሆኜ መፈሪያሽ ትምክህትሽ እንዲሆን በኔ
ቢያስብ ቢያልምም እራሴ በራሡ ለራስ ብያኔ
ሰነጋኝ ጣትሽ ጨፍልቆ ካንቺ የዘመድኩት ወንድሜ
ከእጄ ቢያጣ ጠብ-መንጃ ይዞ አሲዞኝ ጉሜ::
አድሬ ላይቀር መንቃቴ ሌላ ጨለማን ላልናፍቅ
መጀርጀሬን ባርኪልኝ ቤት መመለስን እስካውቅ
“ካገሩ የወጣ ከቤቱ ካገሩ ደግሞ እስኪመለስ
ቢጭኑት ሚስኪን አህያ ቢጋልቡትም ያው ፈረስ”
ብሎ መፍራቱ ቀርቶብኝ ለማላውቀው ደጅ ቅልማጤ
ለዚህ እንኳን እንትፍ በይልኝ ስደቴ እንዳይሆን ምጤ
ታዲያ ምን ላድርግሽ እናቴ? ሌማትሽ ለኔ ሲርቀኝ
እልፍኝሽ በኔ ላይ ተዘግቶ ገረድ ቤትሽ ሲተርፈኝ
ጤፍሽ ለእኔ ተከቶ በዋሪያት ምግብ ስትሸኚኝ
ልጅ መባሌ ተረስቶ ባዳ ስሆን በቤቴ
መውደዴ ዋጋ ሲያጣ መፈቀር ሲሆን ጥማቴ
ታዲያ ምን ልበልሽ እማማ ላባብልሽ እንዴት አድርጌ?
ልምምጥ አላስተማርሽኝ የጭራ መቁላትን ብላጌ
ተለማምጠሸ አታውቂምና ከደጅሽ ያደረን ሁሉ
እኔም ከቶ አላደርገውም ያንቺው ልጅ ነኝና ቅሉ
የማንነቴ ምዕላድ የምንነቴ ግላጬ
የማህጸንሽ ተቋዳሽ የመታወቂያ ጭላጬ
ነኝ እና ያንቺ ግልባጭ ከ‘ድልሽ እድል ምጣባ
ካመልሽ አመል የምቆርስ ሲወዱኝ የማላውቅ ገሪባ
ባለሽበት ላግኝሽ እናቴ ወንድሜ ወርዶ ከላይሽ
ልጆችሽ በኩብላይ ሳያልቁ ሳይሞት መጻኢ እድልሽ
ደህና ሁኚ እናት አለም ወይኔ ልጆቼ ያስብልሽ
ጡትሽን መጠው አፍልቀው በወተትሽ እንዲያጥቡሽ
ወትሮስ ሲጠቅሱት ያልገባው ቢቆነጥጡት ይረዳ?
ከሜዳ ጠፋ ቢሉ ከጫካ ይሸመት የል እዳ፡፡
4/12/93
ለሊት 8፡00
ቦሌ አይሮፕላን ማረፊያ