ቅዳሜ 27 ኤፕሪል 2013

ደጅ ያደረ ልብ



የልጅነት ህልሜ ጠይሞ መጥቆርሽን ባየው በመልክሽ
ነፍስ አውቄ በዕውን አይኔን ገልጬ ባይሽ
ከፍቅር በቀር ከውስጤ የሚወጣኝ ፍላቂ
አጣሁ በውስጤ ትርጉሙን የመውደዴን ድቃቂ
ከማህጸንሽ በቅዬ ካንቺነትሽ ስር ብገኝም
በስምሽ ስም ገዝቼ ባንቺነትሽ ብጠራም
ቡራኬሽ ባይኖር በላዬ የ“እደግ” ምርቃት ቱፍታሽ
ባትረግሚኝም ቅሉ መኖሬ በዕጆችሽ ጣት ስታሽ
ፍቅሬ ጎመዘዘኝ እናቴ “እማማ” ያልኩሽ አቃረኝ
መውደድሽ ሬት ማቀፍሽ የሾኽ ሆኖ ተሰማኝ::
“ሰው ቦታን ይቀድሳል ቦታ ደግሞ ሰውን ይቀድሳል”
ይሉ ብሒል ጠፋኝ እና አግኝቶ ማመስገንን
ጀረጀርኩ ደጅሽ ላድር ወለለት ባይኖረው ድምጼ
ከጆሮ ደርሶ ባይገባ የእዬዬ ቅላጼ
“እሹሩሩ” መባሉ ቀርቶብኝ በልጅ ወግ መባበሉ
መቅለጥ መቅበጤ ቆይቶ “ስመኽኝ ውጣ” መባሉ
በወጉ ድምጼ ተሰምቶ ከደፍሽ ወድቄ ባደርኩ
የኽው ስልሽ ብተሰሚኝ ባለመስማትሽ ባላዘንኩ::
እናትዬ!
መውደዴ ኪሳራ ብቻ ሲሆን ማፍቀሬ ግርጥጫ
በምን ልታገስ መኖርን በጉስምት በንቅፍት ቁንጥጫ?
አግማስሽ ሆኜ መፈሪያሽ ትምክህትሽ እንዲሆን በኔ
ቢያስብ ቢያልምም እራሴ በራሡ ለራስ ብያኔ
ሰነጋኝ ጣትሽ ጨፍልቆ ካንቺ የዘመድኩት ወንድሜ
ከእጄ ቢያጣ ጠብ-መንጃ ይዞ አሲዞኝ ጉሜ::
አድሬ ላይቀር መንቃቴ ሌላ ጨለማን ላልናፍቅ
መጀርጀሬን ባርኪልኝ ቤት መመለስን እስካውቅ
“ካገሩ የወጣ ከቤቱ ካገሩ ደግሞ እስኪመለስ
ቢጭኑት ሚስኪን አህያ ቢጋልቡትም ያው ፈረስ”
ብሎ መፍራቱ ቀርቶብኝ ለማላውቀው ደጅ ቅልማጤ
ለዚህ እንኳን እንትፍ በይልኝ ስደቴ እንዳይሆን ምጤ
ታዲያ ምን ላድርግሽ እናቴ? ሌማትሽ ለኔ ሲርቀኝ
እልፍኝሽ በኔ ላይ ተዘግቶ ገረድ ቤትሽ ሲተርፈኝ
ጤፍሽ ለእኔ ተከቶ በዋሪያት ምግብ ስትሸኚኝ
ልጅ መባሌ ተረስቶ ባዳ ስሆን በቤቴ
መውደዴ ዋጋ ሲያጣ መፈቀር ሲሆን ጥማቴ
ታዲያ ምን ልበልሽ እማማ ላባብልሽ እንዴት አድርጌ?
ልምምጥ አላስተማርሽኝ የጭራ መቁላትን ብላጌ
ተለማምጠሸ አታውቂምና ከደጅሽ ያደረን ሁሉ
እኔም ከቶ አላደርገውም ያንቺው ልጅ ነኝና ቅሉ
የማንነቴ ምዕላድ የምንነቴ ግላጬ
የማህጸንሽ ተቋዳሽ የመታወቂያ ጭላጬ
ነኝ እና ያንቺ ግልባጭ ከ‘ድልሽ እድል ምጣባ
ካመልሽ አመል የምቆርስ ሲወዱኝ የማላውቅ ገሪባ
ባለሽበት ላግኝሽ እናቴ ወንድሜ ወርዶ ከላይሽ
ልጆችሽ በኩብላይ ሳያልቁ ሳይሞት መጻኢ እድልሽ
ደህና ሁኚ እናት አለም ወይኔ ልጆቼ ያስብልሽ
ጡትሽን መጠው አፍልቀው በወተትሽ እንዲያጥቡሽ
ወትሮስ ሲጠቅሱት ያልገባው ቢቆነጥጡት ይረዳ?
ከሜዳ ጠፋ ቢሉ ከጫካ ይሸመት የል እዳ፡፡
4/12/93
ለሊት 8፡00
ቦሌ አይሮፕላን ማረፊያ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ