ሐሙስ 3 ጁላይ 2014





         yg!z@ wdB
m¬mN Æì nW s!kBR xlQ§qE
XWqT JLnT nW s!gN x§êqE
y¸ÃyW xYñRM xÃg"M ¥rG
bzmn sRì ybql CFRG
l[/Y FQR ylM kng\ k#‰Z
mÄB kBé úl ï¬ ylM lxL¥Z
                              2/9/2006

ሰኞ 23 ጁን 2014

እውቀት እንደቀላል ሲጠፋ



ከንባታ ጠንባሮ አካባቢ በስራ ምክንያት ሔጄ ነበር፡፡ ህጻናት ማንበብን አዝናኝ በሆነ መንገድ እንዲማሩ እና እንዲወዱ የሚያደር ስልጠና ለመስጠት፡፡ ስልጠናው ላይ ለህጻናቱ ትምህርታዊ ጨዋታ በሙከራ ደረጃ ቀረበ፡፡ ጨዋታው በአንድ ካርድ ላይ የአንድ እንስሳ ስም በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ እና በከንባተኛ ይጻፋል፡፡ በሌላ ካርድ ደግሞ የእንስሳው ፎቶ ይቀመጣል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተዛጋጁ በርከት ያሉ ምስሎችና ስሞችን በማገናኘት እንደካርታ ጨዋታ በመብላት ነጥብ ማስቆጠር ነው፡፡
በመሐል ያልጠበኩት ነገር ተከሰተ፡፡ ተማሪዎቹ የአንድ በጣም ታዋቂ እንስሳን ፎቶ ተመለከቱ፤ ሆኖም ከተጻፈው ስሙ ጋር ለማገናኘት ተቸገሩ፡፡ ግራ ስጋባ “ይህ እንስሳ ምንድን ነው” አልኳቸው ካርዱን ይዤ፡፡ ሁሉም በእርግጠኝነት እንደማያውቁት ነገሩኝ፡፡ ወጣቷን የልጆቹን መምህርት ጠራኋትና “ይሔ እንስሳ በአካበቢው ቋንቋ ምን ተብሎ እንደሚጠራ ለልጆቹ  ንገሪልኝ” ስል ትብብሯን ጠየቅኩ፡፡ መምህርቷም ስዕሉን እንዳየች ፊቷን አጨፈገገችና “ይሄን እንስሳ ስሙን አላውቀውም፡፡ ግን ሆሳዕና ስሄድ አይቼው አውቃለሁ” አለችኝ፡፡ አሁን በበለጠ በአግራሞት ተሞላሁ፡፡
“እስቲ አባባ ስሙን ሳያውቁት አይቀሩም ልጥራቸው” አለችና በእድሚያቸው ገፋ ያሉትን የትምህርት ቤቱ ሽማግሌ ስከትላ መጣች፡፡ እጄ ላይ ያለውን ስዕል እያሳየሁ የቀድሞውን ጥያቄ ጠየቅኳቸው፡፡ አዛውንቱ ፈገግ አሉና “የዚህ እንስሳ ስም ‘ውሺቾ’ ይባላል፡፡ ያው በአማርኛ ‘ውሻ’ የምትሉት ነው፡፡ ሆኖም በዚህ አካባቢ ውሻ ፈጽሞ አይታወቅም” አሉኝ፡፡
ምክንያቱን ለማወቅ ጓጉቼ ጠየቅኋቸው፡፡ “ከብዙ ዘመናት በፊት በኔ አያት ዘመን የውሻ በሽታ ገብቶ ህዝቡን ፈጀው፡፡ ብዙ ሰው አለቀ፡፡ በዚህ የተነሳ የሐገር ሽማግሌዎች ተሰበሰቡና ‘ውሻ ያሳደገ ውሻ ይውለድ፡፡ በአካባቢ ውሻ ያየ ሁሉ ውሻውን ያባርር’ በማለት አወጁ፡፡ በዚህም ተነሳ ውሻ ከሐገሩ ጠፋ፡፡ ስለዚህ የአካባቢው ህጻናት ብቻ ሳይሆኑ ወላጆቸው ጭምር ወደሌላ አካባቢ ካልሄዱ በቀር ውሻን አያውቁትም፡፡” በማለት አስረዱኝ፡፡  
እንደው እንደዘበት፣ እንደቀላል፣ ‘የሰው ልጅ የመጀመሪያ ወደጅ’ ተብዬው ውሻ መረሳቱ ብቻ አይደለም የደነቀኝ፤ እንዴት በቀላሉ ውሻን ያክል እውቀት ከሰው አምሮ ውስጥ እንደሚጠፋ ማወቄ ጭምር እንጂ፡፡ ከዚህ በላይ ግን አንድ ቁም ነገር መያዝ ፈለግኩ፡፡ የፈራ አለቃ ሁሉ ለጊዜያዊ መፍትሄ የሚወስደው ክልከላ ለትውልድ ትክክል መስሎ እውቀትን እንደሚጋርድ ማሳያ ይሆናል፡፡ ሐገሬ ደግሞ የዚህ አይነት ባህሪ የተጠናወታቸው ከላይ እስከታች ያሉ አለቆች ሞልተዋታል፡፡ ለዛሬ ችግር የትውልድን አዕምሮ የሚደፍኑ!!!

ዓርብ 3 ጃንዋሪ 2014

ድለቃ




ጠርሙስ እያጋጨን
ወይን እየተጎነጨን
ያወራነው ሁሉ ያቀድነው ጠቅላላ
ስለ ዳቦ ቁራሽ ስለ ውሃ አተላ
ስለበደላችን ስለፍትህ ማጣት
ከንቱ ስለጠፋው የሰው ልጆች ህይወት
እስር ስለዋለው ነጻነት ይሉት ሱስ
ዋጋው ስለጠፋ ሰው ስለሚባል ቅርስ
ነበረ ወይ ባክህ? ያወራነው ወሬ
አስታውሰኝ ላስታውሰህ ተዘነጋኝ ዛሬ
ባዶ! ባዶ ጣሳ
ያውም የተበሳ
ባዶ ባዶ ወንፊት
የሚያሳልፍ ምርጊት
ከፊቴ ተቀምጦ
ዝንጋኤ ሞላው ድህነቴ አምጦ፡፡
እውነት እኔና አንተ ወይን ከጨለጥን
ጠርሙስ ከጨበጥን
አንድ መንፈቅ ቀርቶ አንድ ሳምንት ሞላን?
ወይስ ያወራነው
እንዲያ የተከዝነው
ስለህዝቡ ማጣት
ስለሰው መገፋት
ስለፍትህ መጥፋት
ድህነት ተጭኖት መሸነፍን ፈርቶ
በይሉኝታ ብቻ ስለሚኖር ሞቶ
ስለዚህ ሚስኪን ህዝብ ስለዚህ ባተሌ
ስለነዛ መርዛም ስለኒያ አለሌ
አልነበረም ከቶ ወይስ ተሳሳትኩኝ
አንተ ስትደነድን እኔ ኮሰመንኩኝ፡፡
እኔያ እያልኩ ስጠቁም ቅርቤ ርቆብኝ
እንዴት ተቀረጠፍኩ እንዴት ተሸወድኩኝ፡፡
አይደለ አይደለ ወሬያችን ነው ሌላ
ስለሚተኛ ነው ነው ስለሚበላ
የሴቶቹ ዳሌ የመኝታው ምቾት
የአራቱን መናፈቅ የቀለም ቤት ድምቀት
ስለቅንዝር ዓለም ስለፍትዎት ደስታ
ስለዘጠኝ አለም ስለሙሉ እርካታ
ነበር ያወጋነው ብርጭቋችን ሞልቶ
ምላሳችን ታስሮ ህሊናችን ሰልቶ
ነው እንዴ ወዳጄ? ግራ ገባኝ ዛሬ
ድርድር ቦታችንን ብመለከት ዞሬ
በዚህች ቡናኝ ሐገር አቡናኝ በሞላባት
ከድሀ ቀምቶ ሀብታም በኖረባት
ነጻነት በጠማው እስረኛ ነዋሪ
ሌላ አጭር ሰንሰለት የሚያስር ቋጣሪ
ፍትህ በናፈቀው አንጋጣጭ ተበዳይ
የግፍን ተራራ የሚጭን ባናት ላይ
እንዴት ተከሰተ ከቶ እንደምን መጣ
እያልኩ ስደሰኩር እያልክ ስትንጣጣ
የለበስከው ማሊያ መቼ ተቀይሮ
የታፈነን አፋኝ ሆንክልኝ ቀበሮ
የምትገኝ መስሎኝ ከፊት ለተበዳይ
ካሸናፊ መድረክ በቀልክ እንደእንጉዳይ
ለባለድል መዝሙር ለሞላው አጃቢ
አከንፋሹ ሆነህ እብደቱን ጀብጃቢ
ወይንህ ሲጎልብህ የምትጎነጨው
ከፊት ድንገት ወጥተህ ደሀን የምትፈጨው
የፍትህ ናፋቂን ተስፋ የምትቀጨው
ለዛሬ ፍስሐ ለማይዘልቅ ደስታ
ውለህ ለማታድረው ላልገዛኽው ቦታ
ለምትወድቅበት አጥንትህ ተግጦ
ለምትጣልበት ስኳርኽ ተመጦ
ላንድ ቀን ላንድ ዛሬ ነው የተሰለፍከው
የገዳይን ፍትህ ላገር የሰበክከው፡፡
ካዓለም የተማርነው በዘመን ቆይታ
ሌላ ነው ልዩ ነው የእውነት እውነታ
ላሸናፊ መቆም ሆድ ብቻ ይበቃል
ተሸናፊን ማገዝ ወኔን ይጠይቃል፡፡
2005-18/4/2006

ሐሙስ 29 ኦገስት 2013



የሚስኪኖች አመጽ
ሀገር ምድሩ ሁሉ ተሸጦ በገንዘብ
የኛን ስፍራ ማጣት ህዝብ እንዴት ይገንዘብ፡፡
አላይ ላለ አይን ለማይሰማ ጆሮ
አመጽ አንስተናል ከዛሬ ጀምሮ
ካጣን ትንሽ ስፍራ ለመላወሻ እንኳን
ለሚሻግት እህል ማስጫ ከተቸገርን
ምንዱባን ተነሱ አብዮት አቃጥሉ
የደሀ ንብረት ነው የሐብታም ግዛት ሁሉ፡፡
ሰኔ 26/2005

ረቡዕ 24 ጁላይ 2013

የይታገሱ መስኮት: ስለራስ የሳሉትን ምስል ማምለክ እና ራስ የሳሉትን ስዕል መፍራት

የይታገሱ መስኮት: ስለራስ የሳሉትን ምስል ማምለክ እና ራስ የሳሉትን ስዕል መፍራት

ስለራስ የሳሉትን ምስል ማምለክ እና ራስ የሳሉትን ስዕል መፍራት



ሁለት አደገኛ ነገሮችን አውቃለሁ፤ ስለራስ የሳሉትን ምስል ማምለክ እና ራስ የሳሉትን ስዕል መፍራት፡፡ ሁሌ ባየኋት ቁጥር የምትገርመኝ ስዕል አለች፡፡ ስዕሏ መስታወት ፊት የቆመች ድመትን ይዟል፡፡ በመስታወቱ ውስጥ ያለው ምስል ግን የድመቷ ሳይሆን የአንበሳ ነው፡፡ አንዳንዴ አካባቢያችንን ስናስተውል ከሆኑት በላይ ለራሳቸው ስዕል ታላቅነትን የሰጡ ለዛም የተሳሳተ ምስል የሚንበረከኩ በርካቶች ናቸው ፡፡ በፖለቲካውም፣ በመንደሩም፣ በመስሪያ ቤቱም ሆነ በጓደኝነቱ እነዚህን ማግኘት አይከብድም፡፡ እነዚህ ሰዎች “እኔ” ከሚል ቃል የበለጠ የሚያውቁት የሌለ ይመስላሉ፡፡ የሁሉም ነገር ባለቤት እና ፈጣሪ አድርገው ራሳቸውን ያስባሉ፡፡ ሲመስላቸው እነሱ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ምድር እንኳን ምህዋሯን ጠብቃ እንዴት ልትዞር እንደቻለች ይገርማቸዋል፡፡ ያንንም መስማት እሱንም መናገር አይሆንላቸውም፡፡ ሊያወሩም ሆነ ሊናገሩ የሚፈልጉት እነሱ ስላበረከቱት አስቷጽዖ እንጂ ስለሌሎች አበርክቶ አይደለም፡፡
ብዙም ርቀን አንሂድ፤ በቀኝም ሆነ በግራ የተሰለፉትን ፖለቲከኞቻችንን ማየት በቂ ነው፡፡ የነገሮች ሁሉ ቁልፍ የሆኑ መሆኑን ሊነግሩን እና ሊመክሩን ይነሳሉ፡፡ እነሱ ጋ ፈጽሞ መሳሳት ይሉት ታሪክ የሌለ ያስመስሉታል፡፡ የመፍትሄዎች ሁሉ መፍትሄ ከነርሱ ውጪ እንደሌለ ይነግሩናል፡፡ ለመናገር እንጂ ለመስማት ጆሮ የተፈጠረባቸው አይመስሉም፡፡ ስለራሳቸው የሳሉት ስዕልን ተጠራጥረው አያውቁም፡፡ በነሱ መፍትሔ ሐገር የረጋ ህዝብ የተጋ ይመስላቸዋል፡፡ የሚለኩት እና የሚመትሩት እነሱ ካሉበት አቅጣጫ ብቻ ስለሆነ ልዩነቱን መረዳት አይቻላቸውም፡፡ ምናልባት የቆሙበት አላማ የተሳሳተ ሊሆን እነደሚችል ፈጽሞ ማሰብ አይሹም፡፡ ከእውነታው ጋር ሲፋጠጡ ማጥፊያ እንጂ መታጠፊያ መንገድ የላቸውም፡፡
ይህ አይነት ስለራሳችን የተጋነነ ስዕል መስጠት ከአደገኛ በላይ አደገኛ ነው፤ የሰናዖር ውድቀትን ያመጣል፡፡ አለአግባብና አለአቅም አየር ላይ መንሳፈፍ ከእውነተኛው ማንነት ጋር መፋጠጥ ሲመጣ ማረፊያ ያሳጣል፡፡ በራስ መተማመን ደግ ነገር ነው፤ በራስ ማመን (ራስን ማምለክ) ግን ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አንዳንዶች እጃቸው ላይ ያለው ነገር አስተማማኝ እና የማይናድ ይመስላቸዋል፡፡ እውቀት ማለት ያልታወቀ ነገር እንዳለ ማወቅ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም መጠርጠሩ ይበጃል፡፡ የዛሬው ማወቃችን ነገ አላዋቂነት እና የተሳሳተ ሊባል እደሚችል ማመን ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ማመንም ልክ ያስፈልገዋል ከእኔ ርዕዮተ አለም ውጪ ላሳር፣ ከኔ ሃይማኖት ውጪ ዉጉዝ፣ ከኔ ዕውቀት ውጪ ድንቁርና ማለት ራስን ማምለክ ነው፡፡ ትንሽም ቢሆን አቋማችንን መጠራጠር የእድገት እና የእውነት በር ነው፡፡
ሁለተኛው አደገኛ ነገር የራስን ምስል መፍራት ነው፡፡ ይሄኛው ደግሞ በጣም የከረረ ጥርጣሬና ፍርሐት ነው፡፡ ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ያጫወተኝን አንድ ታሪክን ላስቀድም፡፡ በአንድ መንፈሳዊነት በበረታበት ገዳም ውስጥ የነበሩ መነኩሴ ሰይጣን ሁልጊዜ ከጸሎት ሊያስታጉላቸው እንደሚታገል ያምናሉ፡፡ እያንዳንዷም ቀን እንዳትባክን በመጠንቀቅ በማነጋጊያው ላይ ለሚጸለየው ጸሎት ማልደው ጨለማው ሳይወግግ ወደቤተክርስቲያን ያቀኑ ነበር፡፡ አንድ ቀን ቀድመው ተነስተው ከለሊቱ በአስር ሰዓት ወደ ቤተክርስቲያን ያመራሉ፡፡ በበአታቸው እና በቤተክርስቲያኑ መካከል አንዲት ጠባብ ድልድይ አለች፡፡ እዚች ድልድይ ጋ ሲደርሱ ከድልድዩ አቅጣጫ አንድ ጠቆር ያለ ነገር ሲንቀሳቀስ ተመለከቱ፡፡ አባ አማተቡ፤ ያ ነገር ግን አልጠፋም ባለበት ረጋ፡፡ አባ መቁጠሪያቸውን አውጥተው ባሉበት ቆመው ጸሎታቸውን ጀመሩ፡፡ ያሰቡት ሰይጣን ግን ከቦታው አይንቀሳቀስም፡፡ እሱም የድልድዩ መጨረሻ ላይ እንደቆመ ነው፡፡ አባ ውጊያቸውን በማፋፋም መከላከላቸውን አጠናከሩ፡፡ ከማለዳው ጸሎት ያስቀራቸውን ሰይጣን በትጋት ባሉበት ቦታ ቆመው ሳይሸሹ ተዋጉት፡፡ አባ በቆሙበት ጨለማው እየለቀቀ የማለዳውም ጸሎት እያለቀ መጣ፡፡ በብርሐኑ አተኩረው ሲያስተውሉ እሱም እንደሳቸው ከፊቱ የቆመውን ሰይጣን በጸሎት እየታገለ ያለውን የገዳሙን መነኩሴ ተመለከቱ፡፡    
ከመጠን ያለፈ ተጠራጣሪነት ከመዳረሻችን ያዘገየን ወይም ያስቀረን በርካቶች ነን፡፡ ሁሉንም እኔን ለመበደል የተደረገ እኔን ለማዋረድ የተነገረ ነው የምንል ከሆነ አደገኛ ነው፡፡ ይህ ከመጠን በላይ የሆነ መጠራጠር ባልተረጋገጠና እራሳችን በሰራነው ስዕል እየታገዘ የበታችነት ስሜታችንን በማባባስ የቆቅ ኑሮ እንድንኖር ያደርገናል፡፡ እከሌ ይጠላኛል እከሌ ያጠቃኛል ብሎ ማሰብ ሰላም አይሰጥም፡፡ በተለይም ዉሱንነት ላለበት ሰው ራሱን ጠብቆና ደብቆ ላይኖር ነገር ህሌናን ይረብሻል፡፡ ይሔኛው ዘር ይንቀኛል ስለኔ እንዲህ ብሎ ያስባል የሚል የከረረ አመለካከት ደግሞ የባሰ ህዝብን ይበጠብጣል፡፡ በርግጥም እንዲህ ያለ የሐሳብ መረበሽ ያለባቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በስነ አምሮም ጥናትም ራሱን የቻለ በሽታ መሆኑ ታውቆ ህክምና ይሰጣል፡፡ ችግሩ ግን እነዚህ ሰዎች ህመም መሆኑን አያምኑም ፡፡ ጤነኛ መስለው በየቢሮው በኃላፊነት ተቀምጠዋል፡፡ በየመድረኩ ንግግር አዋቂ ተብለው ጥላቻን የሚሰብኩ ህዝብም የሚያዳምጣቸው ናቸው፡፡
እንደነዚ አይነት ራሳቸው የሳሉትን ምስል የሚፈሩ ተጠራጣሪዎች ሊደርሱበት የሚያልሙትን ነገር ከመያዝ ይልቅ በህሌናቸው ከሳሉት ስዕል ጋር ሲላፉ ዕድሚያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ የበዛ ጥርጣሬ ሰላም የለውም፣ በአካባቢው ለሚገኙ ሌሎችም ሰላም አይሰጥም፡፡ እያንዳንዷን ቃል እየሰነተቁ እንዲህ ሊለኝ ፈልጎ ነው እያንዳንዷን የታሪክ ሰበዝ እየለቀሙ ዛሬም እንዲህ ሊያደርጉን አቅደው ነው ማለት እረፍት ያሳጣል፡፡ የዚህ አይነት ሰዎች ጥፋታቸው የትዬ ለሌ ነው፤ ፈሪ ሲደነብር ጀግናን ያስንቃል፡፡
ሐሳቤን ልጠቅልል ለራስ የሰጠነውን ስዕል በማምለክ እና ራስ የሳሉትን ምስል በመፍራት መካከል ያለው ልዩነት በከንቱ መወጠር እና አጉል መኮስመን ብቻ ነው፡፡ በተረፈ ሁለቱም የአንድ ሸማ ሁለት ጥለት መልክ ናቸው፤ የውድቀት ቁልቁለት፡፡  
   

ዓርብ 3 ሜይ 2013

ባለጸጋ ሰው

በምሬት ተሞልተው በአውድ ባደባባይ ሰዎች ይዘልፋሉ
በጓዳ ጎድጓዳ ሌቦች ተደራጅተው ደሀ ይዘርፋሉ
መግቢያ የጨነቀኝ መሸሸጊያ አጥቼ ቆሚያለሁ ካውላላ
ከተደበቀ እውነት ከሰዎች አሰሳ ከእልፍ ምላስ ኋላ
ማነው እኔን ያየ? መልኬን ያስተዋለ ነውሬን የገለጠ
ማነው ሀብቴን ያየ? ከተሸሸገ ሀብት የኔን የመረጠ
ኑልኝ ነጣቂዎች ደሃን አትምዝብሩ ከኔ አለ የላቀ
ዝቃችሁ ማትገፉት የተሸሸገ ሀብት ለአይን የረቀቀ
የያዝኩት በጽኑ ከሌሎች ጠብቄ ከነፍሴ እኩሌታ
አለላችሁ ሀብት አለላችሁ ገንዘብ ለጊዜ ያልተረታ
ሰብ የሚባል ሀውልት ሰው ይሉትን ቅርስ ያጣችሁት ከቶ
እኔ ዘንድ ተኝቷል እናንተ ውስጥ ሞቶ፡፡
ኑልኝ ዘላፊዎች ተጯጯኹ ደግሞ አዲስ ስም ሰይሙ
‘ሰው’ ከመባል ውጪ ለሰው እውነት የለም የሚከብር ስሙ
ስደቡት ይኽን እኔ ‘ሰው’ በሉት ደግማችሁ
ከሰው ተለይቷል ጋርዮሽ ላይ ቆሟል እናንት ሰልጥናችሁ፡፡
ዛሬም “እኛ” ይላል ብቻውን ካውላላ ቆሞ ተገትሮ
አይታችሁ አታውቁም እንዲህ ያል ደንቆሮ::
ተዉ አትድከሙ አይጥበብ ቴራሱ አትሙሉ አደባባይ
ስድቡን የሚጓጓ ስሙ የናፈቀው ቆሟል ካይናችሁ ላይ
ተዉ አትባክኑ ዝርፊያውን አቁሙ ደሀ አይርገማችሁ
ከሁሉ የከበረ ሀብታም ባለጸጋ ሰው እዚህ አለላቹ፡፡
                             26/11/2004